Fana: At a Speed of Life!

ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርትን ሊያቆም ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቦይንግ ከደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርትን በጊዜያዊነት ሊያቋርጥ መሆኑን አስታውቋል።

እንደ ኩባንያው ገለፃ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርት ከፊታችን ጥር ወር ጀምሮ በጊዜያዊነት የሚቆም መሆኑ ታውቋል።

የኩባንያው ቦርድ ለሁለት ቀናት በአሜሪካ ቺካጎ ከተወያየ በኋላ ነው የአውሮፕላን ምርቱ እንዲቆም ውሳኔ ያሳለፈው ተብሏል።

ይህ የሆነውም የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ከአውሮፓውያኑ 2020 በፊት አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ እንዲገቡ ፍቃድ አልሰልጥም ማለቱን ተከትሎ ነው።

የቦይንግ ምርት በሆኑት 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ በደረሰ አደጋ በድምሩ የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትትሎ ካሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ከአገልግሎት ውጭ ተደርገው መቆማቸው ይታወሳል።

አደጋዎቹ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች መቆጣጠሪያ ስርዓት ላይ በነበረ ችግር መፈጠሩ የተገለፀ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ኩባንያው እስከ 9 ቢሊየን ዶላር አጥቷል ነው የተባለው።

ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላኖችን ምርት ቢያቋርጥም፤ ለወታደራዊ ግልጋሎት የሚውለውን የP8 ስሪት ምርቶችን ግን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የቦይንግ አክሲዮን ገበያው እየተቀዛቀዘ ነው የተባለ ሲሆን፥ የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ምርትን ለጊዜያዊነት አቋርጣለሁ ማለቱን ተከትሎ የአክሲዮን ገበያው በ4 በመቶ መቀነሱ ነው የተነገረው።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.