Fana: At a Speed of Life!

ጾታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት እንዲሰጥ የሚያስችል ሕግ ለማውጣት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጾታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት እንዲሰጥ የሚያስችል ሕግ ለማውጣት የግብዓት ማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መከላከልና ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከልና ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚፈጠር መፈናቀል ሴቶችን ለፆታዊ ጥቃት ይበልጥ እንደሚያጋልጥ እና እያጋለጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ባለማወቅ፣ በድፍረት፣ ከስርዓተ ፆታ እኩልነት ልዩነት ጋር ተያይዞ እንዲሁም ሴት ልጅ ላይ ጥቃት ማድረስን የተለመደ አድርጎ መውሰድ የፆታዊ ጥቃት መንስዔ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሴትን ልጅ መላከፍ ጥቃት ማድረስን የተለመደ አድርጎ የመውሰድ አብነት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ከፍ ወዳለ  ጥቃት ሊያመራ እንደሚችልም አስገንዝበዋል፡፡

ይህንን በመከላከል ረገድም ሆነ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስትዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከስራዎችም ውስጥ ተጠያቂነትን ከማስፈን እና ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን መሰረት ያደረገ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል በፍትህ ሚኒስቴርና በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ሀገራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ይህም አስተባባሪ ኮሚቴ አቅጣጫዎችን የሚሰጥና መሰራት ያለባቸው የስትራቴጂ ጉዳዮችን የሚያስቀምጥ ነው ብለዋል አቶ ዘካሪያስ ፡፡

ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ለፆታዊ ጥቃት የሚጋለጡ ሴቶችና ህፃናት ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ የህግ ጥበቃ እንዲኖራቸው እየተደረገ መሆኑንና ሌሎች የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጾታዊ ጥቃት አድራሾቹ ላይ አስተማሪ ቅጣት እንዲሰጥ የማድረግና ያለውን የህግ ክፍት ለመሙላትም ጥናት እየተደረገ እና ግብዓት እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ግብዓት ተሟልቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚላክ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥቃት እየተስፋፋ እንደሆነና እሱን ያካተተ የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ወንዶችን ያሳተፈ ስራ በየጊዜው ንቅናቄ እንዲሁም ግንዛቤ የመፍጠር መድረክ እየተዘጋጀ እንደሆነም አክልው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች የሴት ልጅ ጥቃት የተወገዘ መሆኑን በአስተምህሮታቸው አካተትተው ምዕመናንን እንዲስተምሩ እተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ጥቃቱን አምነው እንዲቀበሉ እና ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ዝም እንዲሉ እየተደረገ ስለሆነ እሱ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያስጠናው እና ከሁለት ወር በፊት ይፋ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ ከ100 ሴቶች 20ዎቹ የተለያየ አይነት ጥቃቶች እንደሚደርስባቸቀው ያሳያል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ቅኝት በፈረንጆቹ 2016 ባጠናው ጥናት ከ100 ሴቶች 35ዎቹ የተለያየ አይነት ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው ማሳየቱን አስታውሰዋል።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.