Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቻይናውያን ባለሀብቶች ዋነኛ መዳረሻ ሆነዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቻይናውያን ባለሀብቶች ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከያንግ ይሃንግ (ዶ/ር) ጋር በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና የቻይናውያን ባለሃብቶች ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክን የማስፋፊያ ግንባታ ለማስጀመር ከኤምባሲው ጋር በትብብር በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል ፡፡

የአዳማ ሁናን ፕሮጀክት የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ሲሆን አሁን ላይ ለግንባታው የሚያስፈልገው 125 ሄክታር መሬት ዝግጁ መደረጉንም ዋና ስራ አስፈጻሚው በውይይቱ ወቅት አንስተዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ማፅናት እንደሚገባ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና የቻይናውያን ባለሀብቶች ተሳትፎ በአብነት የሚነሳ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.