በአማራ ክልል ከለማው የሩዝ ሰብል 14 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2016/17 የመኸር ወቅት ከለማው የሩዝ ሰብል 14 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማን የሩዝ ሰብልን እየጎበኙ ነው።
በጉብኘቱ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት፤ በክልሉ በደቡብ፣ ማዕከላዊ ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል ለምቷል።
ከዚህ ውስጥ ከ71 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማው የሩዝ ሰብል በደቡብ ጎንደር ዞን የለማ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በመኸር ወቅት በሩዝ ሰብል የለማው መሬት በ2015/16 የምርት ዘመን ከለማው ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ ከዚህም ከ14 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡