ሩሲያ እና ቻይና በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣሉ የተወሰኑ ማዕቀቦች እንዲነሱ ሃሳብ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እና ቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኮሪያ ላይ ከጣላቸው ማዕቀቦች ውስጥ የተወሰኑት እንዲነሱ ሃሳብ አቅርበዋል።
ይህም ሰሜን ኮሪያ በኒውክሌር የጦር መሳሪያ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ድርድር እንደ አዲስ በመጀመር አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያበረታታ መሆኑ ተመላክቷል።
እንዲሁም በዋሽንግተን እና ፕዮንግያንግ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና የኮሪያ ልሳነ ምድርን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።
በዚህ መሰረትም ሩሲያ እና ቻይና በሀገሪቱ የባህር ምግቦች እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንዲነሳ ሃሳብ አቅርበዋል።
ከዚህ ባለፈም በውጭ ሀገራት በሚሰሩ የሀገሪቱ ዜጎች ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ እና በፈረንጆቹ 2017 ላይ የተቀመጠው ቅደመ ሁኔታ ተሰርዞ ሰራተኞች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚጠይቅ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል የሚከናወኑ የባቡር እና የመንገድ ትብብር ፕሮጀክቶች ከተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ነፃ እንዲሆኑ የሚል ሃሳብ ተካቷል።
አሜሪካ በበኩሏ በሩሲያ እና ቻይና የቀረበው ረቂቅ በትክክለኛው ጊዜ ያልቀረበ ከመሆኑ ባሻር የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ስትል አጣጥላዋለች።
ስለሆነም የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ጠብ አጫሪ ድርጊቶችን በማከናወን ላይ የምትገኝ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ረቅቁን ውድቅ እንዲያደርግ ነው የጠየቀቸው።
እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ በተመድ የተቀመጠውን ህግ በመጣስ የተለያዩ መጠን ያላቸው ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ከመሞከር ባለፍ በኒውክሌር ድርድር ላይ የምታሳየውን ቸልተኝነት በምክንያትነት አንስታለች።
ምንጭ፦ሬውተርስ እና አልጀዚራ