ኢትዮጵያ ለስታርትአፕ እድገት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራች ነው – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የስታርት አፕ እድገትን የሚያሳልጥ ምቹ ምሕዳር ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ እድገት ተቋማዊና ሕጋዊ አሰራርን የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ውይይት ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት ነው።
የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ለስታርት አፕ ተቋማዊና ሕጋዊ ድጋፍን በመስጠት በኢትዮጵያ የዘርፉን እድገት ማሳለጥ መሆኑ ተገልጿል።
በስታርት አፕ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታትና የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸትም ሌላው የረቂቅ አዋጁ ትኩረት ነው ተብሏል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት÷ ኢትዮጵያ ከድኅነት ለመውጣት እያከናወነች ያለውን ተግባር በቴክኖሎጂና በፈጠራ ለመደገፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የሀገር በቀል ምጣኔ ኃብት ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በሰጠው ትኩረት በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ኢኮኖሚውን እየተቀላቀሉ መሆኑን ጠቅሰው፥ ስታርአፕ የዚሁ አካል እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መንግሥት ለስታርት አፕ በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ተከትሎ አሰራር ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ አዋጁ አሰራሮችን በማሳለጥ ፈጠራን ለማበረታታት ትልቅ ፍይዳ እንዳለው ተናግረዋል።