ህብረተሰቡ ሪሊፍ የተባለ ህገ ወጥ መድሃኒት ከመጠቀም እንዲቆጠብ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ ሪሊፍ (RELIEF) የተባለ ህገ ወጥ መድሃኒት ከመጠቀም እንዲቆጠብ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስጠነቀቀ፡፡
ባለሥልጣኑ RELIEF የሚባል ሕገወጥ መድኃኒት በውስጡ ዲክሎፌናክ፣ ፓራሲታሞል፣ ክሎረፊኒራሚን እና ማግኒዥየም ትራይሲሊኬት እንዳለው ስለሚገመትና ለጤና ጎጂ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ስላለ መድሃኒቱ ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት አስጠንቅቋል፡፡
መድሃኒቱ በኢትዮጵያ ገበያ በስፋት እየተዘዋወረ መሆኑን ጠቁሞ፤ መድኃኒቱ በሕጋዊ መንገድ በባለስልጣኑ ያልተመዘገበ በመሆኑ ጥራቱ፣ ደህንነቱና ውጤታማነቱ አይታወቅም ሲል አስገንዝቧል።
በተጨማሪም የዚህ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድካም፣ የእይታ መዛባት፣ መፍዘዝ፣ ራስ ምታት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የጉበት ኢንዛይሞች መጨመርና ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል የኩላሊት ጉዳትን እንደሚያመጣም ተመላክቷል፡፡
ይህንን መድኃኒት ለረጅም ጊዜ መጠቀም ከባድ የጉበት፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የልብ ድካም እና ስትሮክ የመያዝ እድልን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡንም የባለስልጣኑ መረጃ ገልጿል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን መድኃኒት ከመጠቀም እንዲቆጠብ እና መድኃኒቱን ጥቅም ላይ ሲውል ከተገኘ በነጻ ስልክ ቁጥር 8482 በመደወል ለባለስልጣኑ ወይም ለክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላት እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርቧል።