አዋጁ ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት፣ በጥራት እንዲፈፅሙ ያስችላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት፣ በጥራትና በውጤታማነት እንዲፈፅሙ የሚያስችል መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ ባካሔደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞችን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂት አዋጅ መርምሮ አጽድቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በአዋጁ አላማና አስፈላጊነት ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የአዋጁ መሻሻል ለተገልጋዮች የተሳለጠና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ ቀልጣፋና የዘመነ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሲቪል ሰርቪሱ ለሀገር እድገት የላቀ ሚናውን እንዲወጣና በመንግስት ሰራተኞች መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር ለመፍጠርም ያለመ ነው ብለዋል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተልዕኳቸውን በብቃት፣ በጥራትና በውጤታማነት እንዲፈፅሙ አዋጁ መልካም እድል የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል።
የሰው ሃብት ምልመላና ቅጥር ክህሎት፣ እውቀትና ብቃትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚያደርግ ስለመሆኑም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡