ከተሞች የብልፅግና ተምሳሌት እንዲሆኑ ነዋሪዎች መትጋት አለባቸው- አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በሚከናወነው ሥራ ነዋሪዎች በባለቤትነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በዎላይታ ሶዶ ከተማ የከተሞች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች የህዝብ ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በዚሁ ወቅትም አቶ ጥላሁን የውይይቱ አላማ ዎላይታ ሶዶ ከተማን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ከከተማዋ ነዋሪዎች በሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በከተማዋ ትናንት ምን ሰራን፣ ለዛሬ ምን ታቀደ፣ ነገ ከተማዋን ለማሳደግ የምናልመው ምንድነው የሚለው ጉዳይ ላይ መወያየት እና መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከተሞችን ማሳደግ፣ ለኑሮ ምቹ እና ተስማሚ ማድረግ እንዲቻልም÷ ዋጋ መክፈል፣ መስራት፣ እና መድከም ያስፈልጋል ማለታቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከሰላምና ደህንነት አኳያ እንዲሁም ከተማን ውብና ማራኪ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች በዋናነት በነዋሪው ባለቤትነት የሚከናወኑ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡