በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረውን የግሪሳ ወፍ መንጋ ከ90 በመቶ በላይ ማስወገድ ተቻለ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሦስት ዞኖች ከተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ መካከል ከ90 በመቶ የሚልቀውን የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ማስወገድ መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ከመስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 6 ወረዳዎች ውስጥ የግሪሳ ወፍ መንጋ ተከስቷል፡፡
በወረዳዎቹ ውስጥ ባሉ 19 ቀበሌዎች የተከሰተው የግሪሳ ወፍ በቁጥር 28 ሚሊየን እንደሚገመት ጠቅሰው÷ ከዚህ ውስጥ ከ21 ሚሊየን በላይ ያህሉን በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት በማካሄድ ማስወገድ ተችሏል ብለዋል፡፡
የኬሚካል ርጭቱ በ356 ነጥብ 5 ሔክታር ላይ መከናወኑን እና ለዚህም 703 ሊትር የግሪሳ ወፍ መካለከያ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን አንስተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት እስከ አሁን በተከናወነው ሥራ ከተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ 90 በመቶ የሚሆነው በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መካላከል መቻሉን ገልጸው÷ የፌደራል መንግሥት የአውሮፕላን፣ ኬሚካል እና ባለሙያዎች ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
አሁንም ቀሪውን የግሪሳ ወፍ መንጋ የመካለከል ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን እና ሥራውም ስኬታማ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው