የፍልሰት ችግርን ለመቅረፍ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የፍልሰትን ችግር ለመቅረፍ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን መከላከልን ጨምሮ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡
አራተኛው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የጋራ የሥራ ቡድን ስብሰባ ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተካሂዷል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚህ ወቅት ÷የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ስትራቴጂክ አጋር በመሆኑ ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣መተላለፊያ እና መዳረሻም ሀገር መሆኗን የጠቆሙት አምባሳደሩ የፍልሰት ጉዳይ ጥንቃቄ ከሚሹ የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር እኩል ሚዛን የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት የፍልሰትን ችግር ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን መከላከልን ጨምሮ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ፍልሰት እና ከፍልሰት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ከጎረቤት ሀገራት እና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሠራች መሆኗንም ገልጸዋል።
በፍልሰት እና ፍልሰት ጉዳይ ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።