በኢኮኖሚ ሪፎርም አፈፃጸም ላይ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ልኡክ ጋር ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) ልኡካን ቡድን አባላት ጋር ተወያተዋል፡፡
በውይይታቸው ኢትዮጵያ ተግባራዊ ባደረገችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አፈፃጸም ዉጤቶች እና በቀጣይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ መንግስት በጥልቀት ተግባራዊ ማድረግ በመጀመሩ እምራታዊ ዕድገት እየተመዘገበ እንደሆነ ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህ ረገድ አይ ኤም ኤፍ ቀጣይነት ያለዉን ድጋፍና ትብብር ማድረጉን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የንግድ ሥርዓት ላይ ስለተወሰዱ ማሻሻያዎች እና ሰለተመዘገቡ አበረታች ዉጤቶች፣ የአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ሂደትና ተያያዥ ጉዳዮች፣ የወጪና ገቢ ንግድ የሚመራበት ስርዓት በህግና አሠራር እየተደገፈ ያለበት ሁኔታ፣ የሀገር ዉስጥ ገበያ ዋጋ ማረጋጊያ እርምጃዎች ዉጤታማነት እንዲሁም የንግድና ኢኮኖሚ ዝረዝር ሪፎርም አፈፃጸሞችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡