Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 6 ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ዕድገት ታይቷል- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድስት ዓመታት እየተወሰዱ በሚገኙ የኢኮኖሚ ማሻሻዎች የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች እድገት ታይቷል ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተሠሩ ሥራዎች እና በቀጣይ መሠራት የሚገባቸው ተግባራት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።

በዚሁ ወቅትም ሚኒስትሯ÷ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ላይ ባለማተኮሯ በ60 ዓመታት የሚጠበቀውን ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት ሳታሳይ ቀርታለች ብለዋል፡፡

ባለፉት 60 ዓመታት ኢኮኖሚዋ በአማካኝ 4 ነጥብ 2 በመቶ ቢያድግም የሕዝብ ቁጥሯ ያደገውን ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት አለመምጣቱንም አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት ሥድስት ዓመታት እየተወሰዱ በሚገኙ የኢኮኖሚ ማሻሻዎች የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ዕድገት ታይቷል ነው ያሉት፡፡

በለውጡ ዓመታት በአማካኝ የ7 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን አንስተው÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሩብ ዓመት አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በኢኮኖሚው ላይ አበረታች ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ለኢኮኖሚው ሽግግር መሳካት የአምራች ዘርፉን ማብቃት እና ድጋፍ ማድረግ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው÷ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ውጤታማ ለማድረግ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እየሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በአሸናፊ ሽብሩ እና ፍቅርተ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.