Fana: At a Speed of Life!

የኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንደሚደግፉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኖርዲክ ሀገራት ኢትዮጵያ ጽዱና አረንጓዴ አካባቢን እውን ለማድረግ የምታከናውነውን ሥራ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

“ትብብር ለለውጥ የኖርዲክ ኢትዮጵያ ውይይት ለተሻለ የውጋጅ አስተዳደር እና የፈጠራ መፍትሄዎች” በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በመድረኩ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ዴንማርክ እና የፊንላንድ አምባሳደሮች ተገኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሃንስ ሄንሪክ ላንድኩዊስት÷ የኖርዲክ ሀገራት የውጋጅ አስተዳደር ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ልማት እውን ለማድረግ እያካሄደችው ካለው ብሄራዊ እንቅስቃሴ ጋር እንደሚጣጣም አስረድተዋል።

የስዊዲን የሪች ፎር ቼንጅ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ መቅድም ጉልላት በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ውጋጅን ወደ ሃብት በመቀየር ላይ የሚገኙ 40 ሥራ ፈጣሪዎችን እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተጀመሩ ሥራዎችን በማስፋት የኢትዮጵያን ከተሞች ንጹህ፣ ጤናማ፣ አረንጓዴ እና ዘላቂ ለማድረግ በመካሄድ ላይ ያሉ ተግባራትን እንደሚደግፉም ቃል ገብተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ÷ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ እና ማራኪ በማድረግ ሂደት ተረፈ ምርቶችን ወደ ሃብት ለመቀየር ሰፊ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ከኖርዲክ ሀገራት ጋር የተጀመረው ትብብርም ዓለም አቀፍ ልምዶችን ለመቅሰም ወሳኝ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

አዲስ አበባ በአስገራሚ ፈጣን ለውጥ ላይ ነች ያሉት የኖርዲክ ሀገራት አምባሳደሮች÷ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የአረንጓዴ ልማት ተግባራት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.