የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያን ያሻገሩ መሆናቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በውስብስብ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊው አውድ ውስጥ የተካሄዱት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያን ያሻገሩና ያጸኑ መሆናቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) እና ሌሎች አባላት እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስትራቴጂክ አመራሮች በተገኙበት መድረክ የተቋሙ የሦስት ወር እቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡
በግምገማው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን÷ ተቋማዊ ሪፎርሙ ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ባጋጠማት ወቅት ጭምር ሲከናወን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይም ተቋማዊ ሪፎርሙ ከወቅታዊ የደኅንነት ስጋቶች አንጻር የተቃኙ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡
ባላፉት ሶስት ወራት የሁኔታ ትንተናዎቹን መሰረት በማድረግ በተከናወኑ የመረጃ እና ደህንነት ስራዎች ሊከሰቱ ይችሉ የነበሩ የጸጥታና የደኅንነት ስጋቶችን ቀድሞ በማወቅ መከላከል መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስትራቴጂክ አመራሮች በበኩላቸው÷ ሪፎርሙ በተቋምና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፤ ከውጭ አቻ ተቋማትና ከሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በአጋርነት እየተተገበረ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም መረጃ የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ ማምጣቱን ነው የገለፁት፡፡
የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው÷ በርካታ ፈተናዎች ባሉበት ቀጣና የተደረገው ሪፎርምና የተገኘው ውጤት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሪፎርም ሥራዎቹ ኢትዮጵያን ያሻገሩና ያጸኑ መሆናቸውን ገልጸው÷ ይህ ስኬት የመጣው በተግባር የተፈተኑ ቁርጠኛ የለውጥ አመራሮች እና የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሀገራዊ መንፈስ የሚወጡ ሠራተኞች በመኖራቸው ነው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሩን ክፍት በማድረግ ሕዝባዊ ተቋም መሆን መቻሉን ጠቅሰው፤ በሪፎርሙ ብዝሃነትን ያረጋገጠ ተቋም ለመገንባት የተሄደበት ርቀትና የተገኘው ስኬት እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ተቋሙ የደኅንነት ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየትና ስምሪት በማድረግ ረገድ፤ ቅንጅታዊ አሠራርን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ከበጀት ውስንነት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ማሳሰባቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ አመላክቷል፡፡