ኢትዮጵያ ለሰላምና መረጋጋት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም ለዓለም ሰላምና መረጋጋት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።
በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 27 ከፍተኛ መኮንኖችን በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እንዳሉት፤ በኢንስቲትዩቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ናቸው።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነት እና ግጭት መንሰራፋት ፈተና በመሆኑ በጋራ መቆምን ይጠይቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 75 ዓመታት በተሰማራችበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አኩሪ ድል በማስመዝገብ ለቀጣናውም ሆነ ለዓለም ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለሰላም የምታበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
በሰላምና ግጭት አፈታት አስተዳደር ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ከፍተኛ መኮንኖች የተሰጣቸውን የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና በብቃት የተወጡ መሆናቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የላቀና የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።