የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ ገባ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ መግባቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህንን የገለጹት፤ በነጻ ንግድ ቀጠናው ስራ ለመጀመር ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፍቃድ በማውጣት ሂደት ላይ ያሉ ባለሀብቶች ነጻ ንግድ ቀጠናው እየሰጠ ያለውን የተለያዩ አገልግሎቶች በጎበኙበት ወቅት ነው።
ነጻ ንግድ ቀጠናውን ወደ ተሟላ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት ባለፉት ሶስት ወራት በባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሀብቶቹ ወደ ነጻ ንግድ ቀጠናው ገብተው ስራቸውን እንዲጀምሩ የሚያስችሉ ድጋፎች በሙሉ እንደሚደረጉ ገልጸው፤ የዛሬው የባለሃብቶች ጉብኝት የሚደረገው የድጋፍ ሂደት ማሳያ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ሀገር አቀፍ የነፃ ንግድ ቀጠና ትግበራ ኮሚቴ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴን በመገምገም ነጻ ንግድ ቀጠናው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ ተገቢውን ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱም ተመላክቷል፡፡