Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራና አካባቢ ጥበቃ ሥራ የሚያሳይ መካነ-ርዕይ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዘርባጃን ባኩ እየተካሄደ ባለው የኮፕ29 ጉባዔ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ እና አካባቢ ጥበቃ እየሠራች ያለችውን ሥራ የሚያሳይ መካነ-ርዕይ (ፓቪሊየን) በፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተመርቆ ተከፍቷል።

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል፣ በዘላቂ ግብርና እና በደን ጥበቃ ላይ ያላትን አዳዲስ አቀራረቦች አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማኅበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ ነች ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም ትኩረቱን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በማድረግ ተጨባጭ ድጋፎችን በተለይ ለታዳጊ ሀገራት መስጠት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፍ ትብብር በማድረግ የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባ ገልጸው÷ በተለይም በአፍሪካ ሀገራት ዘላቂ መፍትሔዎችን በማምጣት ረገድ ትብብሩ ያለውን ወሳኝ ሚና ማስገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል አቅርቦት በምግብ ዋስትና፣ በቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የችግኝ ተከላ እና የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችን ያስቀደመ ተግባር እየሰራች ነው ብለዋል።

በኮፕ 29 እየተሳተፈ ያለው የኢትዮጵያ ልዑክ ቁልፍ ውይይቶችን በማድረግ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ እና አካባቢ ጥበቃ ተሞክሮ እንደሚያካፍል ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.