2 ሺህ ኪሎ ዋት የሚያመነጨው የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን በቆልማዮ ወረዳ 2 ሺህ ኪሎ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት የምረቃ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ሽፈራው ተሊላ(ኢ/ር) ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል::
በመርሐ ግብሩ ላይ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር )÷ ባለፉት አመታት በኢነርጂው ዘርፍ አኩሪ ስራዎችን መስራት መቻሉን አንስተው ለዚህ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድቡ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደረጃ የፀሀይ ሀይል ማመንጫ በመጠቀም ለህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው÷ ከለውጡ በኋላ በክልሉ 81 ከተሞች የ24 ሰአት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ሽፈራው ተሊላ(ኢ/ር)÷ በሀገሪቱ 13 የፀሀይ ሃይል ማመንጫ ጣቢዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸው ከዚህም ውስጥ 3ቱ በሶማሌ ክልል እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱን ያገኙ የአካባቢው ነዋሪዎችም ለዘመናት ትልቅ ችግር ሆኖባቸው የቆየውን የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል::
የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በወረዳው 16 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን÷ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ መገንባቱ ተመላክቷል፡፡
አምስት የማሰራጫ ትራንስፎርመር ያለው ሃይል ማመንጫው በአሁን ሰዓት ለ380 አባዎራዎች ተደራሽ ማድረግ ችሏል፤60 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎችን የመብራት ተጠቃሚ የማድረግ አቅም እንዳለውም ተመላክቷል፡፡
በዘቢብ ተክላይ