Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የተሰሩት ተርሚናሎች ለትራንስፖርት አገልግሎት መሳለጥ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ የሚገኙት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ምቹ ተርሚናሎች ለተገልጋይ ከሚሰጡት ምቾትና ካላቸው ደህንነት በተጨማሪ ለትራንስፖርት አገልግሎት መሳለጥ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ተገለፀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በመልማት ላይ ያሉ እና ለምተው ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ የአውቶቡስና የታክሲ ተርሚናሎች ይገኛሉ፡፡

ይህንን አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየታቸውን የሰጡት የታክሲ ተራ አስከባሪዎች፣ ሾፌሮችና ተሳፋሪዎች አዲስ የተገነቡት ተርሚናሎች እጅግ ምቹና ዘመናዊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአንድ ጊዜ 11 አውቶቡሶችን የመያዝ አቅም ያለው ሜክሲኮ ሱዳን ኤምባሲ አካባቢ የሚገኘው ተርሚናል ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ቀደም ሲል የነበረውን መጨናነቅ ማስቀረቱን ጠቁመዋል።

ቦታው ምቹና ሰፊ በመሆኑ በፊት የነበረውን መተፋፈግና የደህንነት ስጋት አስቀርቷል ብለዋል።

በፊት የነበረው የአውቶቡስ መያዣ ቦታ መንገድ ዳር ያለ ጠባብ እና የተጨናነቀ በመሆኑ ለዝርፊያና ለትራፊክ አደጋ የሚዳርግ እንደነበር አስታውሰው፤ ተርሚናሉ ይህንን ሁሉ ያስቀረ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ተሳፋሪው አውቶቡሶችን ለመጠበቅ ማረፊያዎች የተሟሉበት እና መፀዳጃ ቦታዎች ያሉት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ምቹ እንደሚያደርገው ነው የገለፁት፡፡

በተጨማሪ ቄራ አካባቢ ለ24 መኪናዎች በአንድ ጊዜ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና 110 ታክሲዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችለው ተርሚናል እና ፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ይህንን እስመልክቶም አስተያየታቸውን የሰጡ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች፣ ሾፌሮችና ተሳፋሪዎች አዲስ የተገነቡት ተርሚናሎች ምቹና ፅዱ በመሆናቸው በትራንስፖርቱ ዘርፍ ይታይ የነበሩ መጉላላቶችን ያስቀሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተርሚናሉ ለተሳፋሪውም ሆነ ለተሽከርካሪ በበቂ ሁኔታ ቦታ መመቻቸቱን ጠቅሰው፤ አሁን ያለውን ንጽህና በመጠበቅ ማስቀጠል የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.