Fana: At a Speed of Life!

የኮፕ29 ጉባዔ ውሳኔዎች ለአየር ንብረት ቀውስ ምላሽ ይሰጡ ይሆን?

አዲ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ምድራችን የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ጫና ቀውስ ውስጥ ከገባች ውላ አድራለች።

የተራዘመ ድርቅ፣ ከልክ ያለፈ ዝናብ፣ ጎርፍ፣ ውሽንፍር የቀላቀለ አውሎ ንፋስ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ የምድር ስነ-ህይወት መቃወስ የተለመደ ሆኗል።

ይህንን ችግር ለመፍታት በማለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚመክረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) በአዘርባጃን ባኩ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል።

የአየር ንብረት ትንታኔ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኑት ቢል ሀሬ፥ የምድር እጣ ፈንታ በሚቀጥሉት አምስትና 10 ዓመታት በኮፕ29 ጉባኤና በሀገር ደረጃ በሚወሰድ እርምጃ ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመላመድ እና ችግሩን ለመቅረፍ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ለመደገፍ ትሪሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ አንፃር ብቻ ሲታይም አስቸኳይ መፍትሄን ካልተወሰደ ምድር ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከበርካታ ትሪሊየን ዶላሮች ይበልጣል ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

አፍሪካ ኒውስ በዘገባው እንዳነሳው አሁን ላይ ትልቁ ፈተና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሚሆን ድጋፍ ማግኘት ሲሆን፥ በዓመት የሚመደበው 100 ቢሊየን ዶላር በቂ እንዳልሆነ የሚሞግቱት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ዓመታዊ በጀቱ 1 ትሪሊየን ዶላር መሆን አለበት ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

በአዘርባጃን ባኩ የሚካሄደው ኮፕ29 ለዚህና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.