የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 729 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ያስመረቀው ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ባለው የትምህርት ደረጃ ያስተማራቸውን ሲሆን፤ በህክምና፣ በምህንድስና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር ክፍል መረጃ እንዳመለከተው፤ 1 ሺህ 942 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው።
ከተመራቂዎቹ ውስጥ 28 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው መረጃ አመልክቷል።