አቶ አረጋ ከበደ ከጎንደር ከተማ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በወቅታዊ የጸጥታና የልማት ሥራዎች ላይ ከጎንደር ከተማ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማዋ አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ተከትሎ በፌደራል መንግስትና በክልሉ ትብብር የልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው÷ በቀጣይ ብርቱ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።
የከተማው ማሕበረሰብ የሰላም ሁኔታው ዘላቂ እንዲሆን ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከሰላሙ ሥራ ጎን ለጎን ለዘላቂ የልማት ሥራዎች መጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንዳለበት ጠቁመው÷የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በከተማዋ የእገታ ወንጀል መበራከት ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን የገለፁት ተሳታፊዎቹ÷ አጥፊዎችን መንግስት በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በምናለ አየነው