የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን በአንድ ቋት መመዝገብ የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት ስራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን በአንድ ቋት መመዝገብ የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት የሙከራ ስራ ጀምሯል፡፡
በዚሁ ወቅት የሴቶችና ማህራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ÷የዲጂታል ስርዓቱ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን መረጃ በትክክል ለመመዝገብና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ሥርዓቱን ሚኒስቴሩ ከሕንዱ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በትብብር የዘረጋው መሆ ኑን ጠቅሰዋል፡፡
የዲጂታል ሥርዓቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግስትና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት የማህበራዊ አገልግሎቶችን በቀጥታ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የሚጠቀሙበትን ‘ኦፕን ጂ2ፒ” ፕላትፎር በመጠቀም በነፃ የተዘረጋ ነው ብለዋል፡፡
መረጃ ሃብት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታዋ÷የተደራጀና አሁናዊ መረጃ መያዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመስጠት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሙከራ ስራው የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎችን በመመዝገብ የተጀመረ ሲሆን ÷የብሄራዊ መታወቂያ ለተመዝጋቢዎቹ ልዩ የመለያ ቁጥር በመስጠት የተጠቃሚዎችን ድግግሞሽ በማስቀረት ድጋፍ ማድረግ እንደቻለ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር አቶ ዮዳህ ዘሚካኤል በበኩላቸው÷ፋይዳ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ የማህበራዊ አገልግሎቶችን የተሳለጠ ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።