Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ንቅናቄን ለመደገፍ ቁርጠኝነቷን በድጋሚ ገለጸች

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ንቅናቄን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቦት ናህያን ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ሼክ ሻክቦት ናህያን፥ ጉባኤው በዓለም የሚከሰቱ አስቸኳይ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ትብብርን የሚያጎላ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት አድንቀው፥ ለዘላቂ እድገትና ብልጽግና ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ ከፍተኛ የአየር ንብረት ውጥኖች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥም ሆነ በቀጣናዊ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ሀገራቸው ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን በማሳደግ ድህነትን ለማጥፋት ሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ አንስተው፥ በኦሞ ወንዝ አቅራቢያ በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።

የአፍሪካን ሰፊ የግብርና አቅም በማጉላት በምግብ ዋስትና ላይ ስለሚኖሩ ቀጣይ ፈተናዎች ገልጸው፥ “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ አጋርነትን ለማጎልበት እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ እንደ ወሳኝ መድረክ ሆኖ ያገለግላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በ2024 የአየር ንብረት እና የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመቅረፍ 4 ነጥብ 86 ቢሊየን ዶላር በማፍሰስ ግብርናን ለማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምርትን በማስተዋወቅ፣ ብክነትን በመቀነስና አደጋዎችን ለመቆጣጠር ስትራቴጂው ትኩረት ማድረጉን አብራርተዋል።

የዓለም ሀገራት የትብብር እና የአብሮነት መንፈስ እንዲጎለብትም ጥሪ አቅርበዋል።

በወንድወሰን አረጋኽኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.