የባሕር ዳር ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕር ዳር ከተማ ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የዜጎች ደህንነት አደጋና አለመረጋጋት በከተማዋ ሰፍኖ መቆየቱና ይህንን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስም መሰራቱ ተመላክቷል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ ጌትነት አናጋው÷በተደጋጋሚ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ በሌላቸው ታዳጊዎችና መምህራን ላይ ጥቃት ሲደርስ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የሐይማኖት አባቶች ታግተው ገንዘብ ከፍለው እንደተለቀቁ ጠቅሰው÷የሽብር ሥራ ውስጥ የገቡ ቡድኖች የንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ጫና በማሳደር ብዙ አልሚዎች ከተማዋን ለቀው ለመሄድ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
በዚህም የጸጥታ ሃይሉን አቅም በማሳደግ በከተማዋ በዝርፊያ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘትና የሥራ ሃላፊዎችን ለማሸማቀቅ የፖለቲካ ተልዕኮ ይዘው ይንቀሳቀሱ የነበሩ 121 አጋቾች ባለፋት ቀናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ወደ ከተማዋ የሚያመሩ ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት ምንም አይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የተሞከረ ቢሆንም በተቀናጀ የፀጥታ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሴራው እየከሸፈ እንዲመጣ አድርገናል ነው ያሉት።
ከተቋማትና ከግለሰቦች የተዘረፉ 10 መኪናዎች ተይዘዋል ያሉት ሃላፊው÷የገጠመውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከጸጥታ ሃይሉ በተጨማሪ ሕዝቡን በማሳተፍ ሕዝባዊ የሰላም ውይይቶች መደረጋቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው ÷የፀጥታ ተቋሙን መልሶ የማደራጀት ሥራ መሠራቱ ከተማዋ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመከላከል አቅም እንዲያድግ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ከፖሊስ በተጨማሪ በሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ላይም ሪፎርም በማድረግ የፀጥታ ሥራውን በተሟላ አቅም መፈጸም የሚችል ሃይል ማደራጀት እንደሚገባም ተነስቷል።
በደሳለኝ ቢራራ