የወጪና ገቢ ንግድ የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩብ ዓመቱ የወጪና ገቢ ንግድ የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማቱ የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡
በዚሁ ወቅትም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ መሰረተ-ልማቶችን የማስፋፋት፣ በሀገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት፣ የገቢና ወጪ ዕቃዎችን ጭነት የማሳለጥ፣ የባቡር መስመር እና መሰረተ-ልማት ተደራሽነትን የማረጋገጥ፣ የመንገደኞች እና የጭነት ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን የማሳደግ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም በሎጂስቲክስ ዘርፍ የኤክስፖርት ኮንቴይነራይዜሽንን የማሳደግ፣ የወጪና ገቢ ንግድ የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥን ጊዜን ማሳጠር፣ ወጪን መቀነስ እና ቅልጥፍናን ማምጣት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
ተጠሪ ተቋማቱ የዕቅዳቸውን ከ92 በመቶ በላይ በማሳካት አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መሠረታዊ ለውጥ እንደታየበት ተጠቅሷል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ፤ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጎለብቱ አሳስበዋል፡፡
ቅንጅታዊ አሠራሮች እንዲጎለብቱ፣ ሀገሪቱ ያስመዘገበችው የሎጂስቲክስ አፈፃፀም ምጣኔ ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የወጪ ንግድን የሚያሰናክሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በትኩረት እንዲሠራ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የሎጂስቲክስ መሰረተ-ልማት ማዕከል ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ፣ የሀገሪቱን እድገትና ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የወደብ አማራጭ የማስፋት ሥራ መሠራት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት፡፡
በተጨማሪም ለአነስተኛ አውሮፕላኖች ማሳረፊያ የሚሆኑ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡