Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ወንጀል የተከሰሱ የፐርTዝ ብላክ ሰራተኞች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመኖሪያ ቤት ሽያጭ ጋር ተያይዞ በማታለል ሙስና ወንጀል የተከሰሱ የፐርTዝ ብላክ ሰራተኞች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዘዘ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የፐርTዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ/ማ የቦርድ አባልና ዋና ስራ አስፈጻሚ እነ ፍስሐ እሽቱን (ዶ/ር) ጨምሮ በ10 ግለሰቦች ላይ እና በሁለት ድርጅቶች ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሾች 1ኛ ፐርTዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ/ማ የቦርድ አባልና ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሐ እሽቱ (ዶ/ር)፣ 2ኛ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ኤርምያስ ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ 3ኛ ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር እና የቦርድ አባል ወ/ሮ ኤፍትታን ነጋሽ (ሶፍያ ነጋሽን) ጨምሮ 10 ግለሰቦች እንዲሁም ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ እና ኖትር ዲዛይን ኃ/የተ/የግ/ማህበር ናቸው።

በዚህም ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በአንደኛው ክስ ላይ ከ1ኛ እስከ 9ኛ ባሉ ተከሳሾች ላይ እንደተመላከተው በ1996 ዓ.ም የኢፌዲሪ የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) እና (ለ) እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ ይገኝበታል።

ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ ከተማ መሃል ሜክሲኮ ላይ በ100 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ባለ 3 መኝታ ቤት በ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚሸጥ መሆኑን በሚዲያ በማስተዋወቅ ሰዎች ቤት ለመግዛት በሄዱበት ጊዜ “መጀመሪያ ገንዘቡን አስገቡና ውሉን ትመለከታላችሁ” በማለት ከሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን አሳሳች ቃላቶችን በመጠቀም፣ ሰዎች ገንዘቡን ካስገቡ በኋላ ደግሞ የአክሲዮን ግዢ ውል እንዲፈርሙ በማድረግ ምንም አይነት የግንባታ ቦታ ባልተረከቡበት ሁኔታ 2 ቢሊየን 234 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በመሰብሰብ ቤቱን ሰርተው ሳያስረክቡ በመቅረትና ግማሹን ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሸሽ አድርገዋል በሚል በየደረጃው ተደራራቢ ዝርዝር ክሶችን አቅርቦባቸዋል።

የቀረበው ክስ ዝርዝር ችሎት ለቀረቡ 4 ተከሳሾች እንዲደርሳቸውና ክሱን በንባብ እንዲሰሙ የተደረገ ሲሆን ቀሪ ተከሳሾችን ግን የአዲስ አበባ ፖሊስ አለማግኘቱን ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አላገኘኋቸውም የሚል መልስ ቢሰጥም በተከሳሽነት የተካተቱ የድርጅት ስራ አስኪያጆች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ በቀጥታ ለጠበቆች ውክልና የሰጡና በቢሯቸው የሚገኙ ተከሳሾች መኖራቸውን ጠቅሶ በፖሊስ የተሰጠው መልስ ተገቢ ጥረት ያልተደረገበትና አግባብ ያልሆነ መሆኑን አብራርቶ ያልቀረቡ ተከሳሾችን ፖሊስ በአግባቡ አፈላልጎ ሊያቀርባቸው ይገባል በማለት አስተያየት ሰጥቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ፖሊስ በተገቢ ጥረት አድርጎ ያልቀረቡ ተከሳሾችን አፈላልጎ እንዲያቀርባቸውና ከሀገር የወጡትን ከኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከሀገር መውጣታቸውን የሚገልጽ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውጤት ለመጠባበቅ ለሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.