ዶናልድ ትራምፕ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አነጋጋሪውና አወዛጋቢው ሲሉ ብዙዎች የሚጠሯቸው የ78 ዓመቱ ዶናልድ ጆን ትራምፕ በፈረንጆቹ 1946 ነበር ምድርን የተቀላቀሉት፡፡
አሜሪካዊው ፖለቲከኛ የሚዲያ ሰውና ነጋዴም ናቸው፡፡
በኢኮኖሚክስ ዲግሪያቸውን ከፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ በ1968 በመቀበል፥ በ1971 የቤተሰባቸውን የሪልስቴት ንግድ በፕሬዚዳንትነት የመምራት ስልጣንን ከአባታቸው በመረከብ የንግዱን ዓለም አጧጡፈው እስካሁን ቀጥለዋል፡፡
በሚዲያውም ተሳትፎ የነበራቸው ትራምፕ ዘ አፕረንታይስ የሚል ተከታታይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በፕሮዲዩሰርነት ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡
ትራምፕ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ባለፉት ጊዜያት ታክስ አጭበርብረዋል የሚል ክስ ተከፍቶባቸው መቆየታቸውም ይታወሳል፡፡
በ2016 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂላሪ ክሊንተንን በማሸነፍ አሜሪካን ለአራት ዓመት በመሩበት ወቅት አወዛጋቢና ‘ትራምፕ እንዲህ ተናገሩ… አደረጉ … ወሰኑ’ በሚል ስማቸው በዜና አውታሮች የፊት ገጾች አይጠፉም ነበር፡፡
በ2019 ዩክሬን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን እንድትመረምር ጫና በማድረግ ስልጣንን አላግባብ ተጠቅመዋል በሚል የኮንግረሱን ስልጣን ተጋፍተዋል በሚልና በ2021 አመጽ አነሳስተዋል በሚል የተከሰሱ ብቸኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው ትራምፕ፡፡
ሆኖም ሴኔቱ በሁለቱም ጉዳዮች ነፃ ብሏቸዋል።
ትራምፕ በ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በባይደን ቢሸነፉም፥ ሽንፈታቸውን ለመቀበል ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህም ምርጫው የተጭበረበረ ነው በሚል ውጤቱ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው ደጋፊዎቻቸው በአሜሪካ ካፒቶል በመገኘት ዓለምን ጉድ ያሰኘ ወረራ ፈጽመው እንደነበር የማይዘነጋ ነው፡፡
ከዚያም በመጨረሻ መሸነፋቸውን በመቀበል ለሌላ ምርጫ ዝግጁ እየሆኑ ጠብቀዋል፡፡
አንዳንድ ምሁራን እና የታሪክ ተመራማሪዎች ትራምፕ በግለሰቦችና በተቀናቃኞቻቸው ላይ በሚሰነዝሯቸው ንግግሮች በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከነበሩት ፕሬዚዳንቶች መካከል በጣም አስቸጋሪ እንደሆኑ ይገልጻሉ።
ትራምፕ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደገና እጩ ሆነው ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሀሪስ ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ መቻላቸው ተረጋግጧል፡፡
በ1982 ትራምፕ ከቤተሰቦቻቸው 200 ሚሊየን ዶላር የሚገመተውን የተጣራ ሀብት (በ2023 ከ631 ሚሊየን ዶላር ጋር እኩል የሆነ) ድርሻ በመያዝ የመጀመሪያውን የፎርብስ የሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ መስፈር ችለው ነበር፡፡
በ2024 ደግሞ የትራምፕ ሀብት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር (ከዓለም በሃብታሞች ደረጃ 1 ሺህ 438ኛ) እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከአንድም ሁለት ጊዜ ከግድያ ሙከያ ያመለጡት ትራምፕ፥ በዛሬው ዕለት የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዚዳንት በመሆን ድጋሚ መመረጣቸውን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት ‘አስደናቂ ድል ነው’ ሲሉ ውጤቱን ገልጸውታል።
ማስታወሻ:- የተጠቀሱት ዓመታት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነው።