ከሪፎርሙ በኋላ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ ማደጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ሪፎርም ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ ማደጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ አስታወቁ፡፡
የባንኩ ግብ የፋይናንስና የዋጋ ንረትን ማረጋጋት መሆኑን ጠቅሰው÷ አዲሱ ረቂቅ አዋጅና፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆችም ይህንኑ ግብ ለማሳካት በሚያስችል መንገድ ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው አንስተዋል፡፡
ሀገራዊ ሪፎርም ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ ማደጉንም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የጀመረችው ጥረት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኢኒሼቲቭ ከመጀመሩ ከዓመት በፊት መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት እየወሰዳቸው ባሉ የተለያዩ ርምጃዎች በቀጣይ ወራት የዋጋ ግሽበቱ እንደሚቀንስም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
መንግሥት ክፍት ያደረገው የንግድ እንቅስቃሴ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ካለው አስተዋጽዖ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያውን ለማሳለጥ ሚናው የላቀ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችው ማሻሻያ በቀጣይ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና፣ ወርቅና የቅባት እህል ግብይት በእጥፍ ማደጉን አንስተው÷ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ምርቶች በአንፃሩ መቀነስ አሳይተዋል ብለዋል፡፡
የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሐዋላ የሚላከው ገንዘብ እድገት ማሳየቱንም ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት አሁንም የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በነዳጅ፣ በማዳበሪያ፣ በመድኃኒትና በምግብ ዘይት ላይ ድጎማ ማድረግ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣን የሚወስነው ሕግ ከሁለት ወራት በኋላ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመጠቆም÷ ይህም የባንኩን ተወዳዳሪነት በእጅጉ እንደሚያሳድገው አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የብድር አገልግሎት፣ ዲጂታል ኢንቨስትመንትና ኢንሹራንስን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡