ኢትዮጵያና ባንግላዲሽ የአቪዬሽን አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻል መከሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ባንግላዲሽ የአቪዬሽን አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ የመግባቢያ ስምምነት ለማድረግ ውይይት አድርገዋል፡፡
ምክክሩ ስምምነት በሚደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ ሲሆን፥ በመደበኛ የሥልጠና ፕሮግራሞች፣ ኦዲቶችና በአቪዬሽን ዘርፎች ላይ የአሠራር ደረጃዎችን ማሳደግን ያካትታል ነው የተባለው፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ከባንግላዲሽ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ሊቀ መንበር የአየር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሞነጁር ካቢርና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር በባንግላዲሽ ባደረጉት ውይይት፤ በአቪየሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት መክረዋል።
በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በማሳደግ እና የሲቪል አቪዬሽን ዘርፎች አዳዲስ የልማት እድሎችን ላይ በስፋት መነጋገራቸው ተጠቁሟል።
የሥራ ሃላፊዎቹ ሲቪል አቪዬሽን እና ተዛማጅ ዘርፎችን ለማሳደግ ውጤታማ እርምጃዎችን በመተግበር ረገድ ያላቸውን ፍላጎትም ገልጸዋል።
ኃላፊዎቹ አክለውም፥ ውይይቱ በኢትዮጵያና በባንግላዲሽ መካከል ያለውን የአቪዬሽን ግንኙነት በማጠናከር ለበለጠ ትብብር መንገድ እንደሚከፍት ያላቸውን ተስፋ መግለጻቸውን የዘገበው የባንግላዲሽ የዜና ምንጭ ቢኤስኤስ ነው።