የአዕምሯዊ ንብረት ሳምንት እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃገራዊ የአዕምሯዊ ንብረት ሳምንት እየተከበረ ነው፡፡
ሁነቱ የዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስትና ከጃፓን የፈጠራ ባለቤት ማረጋገጫ ቢሮ እንዲሁም የኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
ለሶስት ቀናት የሚካሄደው መድረክ ከ13 በላይ የኢንተርፕራይዝ ተወካዮች፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮዎች፣ የኢኖቬሽን ኤጀንሲዎችን የሚያሳትፍ ነው።
የእዕምሯዊ ንብረት ተቋማትን በአዕምሯዊ ንብረት ዘርፍ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ ለሀገር ልማት የሚያበረክቱት አስተዋፆ ከፍተኛ በመሆኑ የጋራ ሀገራዊ ግንዛቤ መፍጠር የመድረኩ ዋና ዓላማ እንደሆነ የባለስልጣኑ ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል ገልፀዋል።
በተለይም ዘርፉ የሀገር በቀል ኢኮኖሚን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው÷በቅርቡ ይፋ የሆነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እውን በማድረግ ረገድም በርካታ ዕድሎች ያለው ነው ብለዋል።
የአዕምሯዊ ንብረት ሳምንቱ ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የክህሎት ስልጠና፣ የዓቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫና የፖሊሲ አውጪ አካላት ጋር የሚደረጉ መስተጋብሮችን የሚያካትት መርሐ ግብር ነው።
በመሆኑም በሀገሪቱ ያለውን የአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተሳትፎ በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ድርሻ ያለውና በሚቀጥሉት ቀናት ከአፍሪካ እንዲሁም ከዓለም ሀገራት የሚገኘውን ልምድ በመቀመር በገበያ ተወዳዳሪ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሚታየውን ክፍተት በመሙላት አኳያ አስተዋፆ እንዳለውም ተገልጿል፡፡
በታሪኩ ወ/ሰንበት