Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለሀገራት ዘላቂ ሠላም ዋጋ ከፍላለች – ብ/ጀ ፖውል ንጂማ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ዔፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ዋጋ መክፈሏን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ፖውል ንጂማ ገለጹ፡፡

ከአኅጉራዊና ቀጣናዊ የሰላም ማስከበር ጥምረት ኃይልና ተቋማት ጋር ሆና ሀገራት ጸንተው እንዲቀጥሉና ዘላቂ ሰላማቸው እንዲረጋገጥ እየሠራች መሆኗንም ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

በተለይም ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ዋጋ መክፈሏን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ የምጣኔ ሃብት እድገትን ለማረጋገጥ የአባል ሀገራት ሚና ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያም ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የእርስ በርስ ግጭት፣ የሃብት አጠቃቀም፣ በቀይ ባሕር የሚስተዋለው ውጥረት ቀጣናውን እየፈተኑ ካሉ የጸጥታ ስጋቶች መካከል መሆናቸውንም ዘርዝረዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በአባል ሀገራቱ መካከል ቅንጅትና ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ለውጥ በማድረግ ጠንካራ ተቋም እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ በዚህ ሂደት ትልቁን ሚና ትጫወታለች ብለዋል።

የመካከለኛው አፍሪካ ጥምር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ንዱውሙንሲ ኦዳስ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና ሰላምን በማስከበር ጉልህ ዐሻራ አላት ብለዋል።

በአኅጉሪቱ ሰላምና ጸጥታን በማስከበር ከውጭ ጣልቃ ገብነትና ጥገኝነት ለመውጣት አንድ የጸጥታ ኃይል መገንባት ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባም ነው ኃላፊዎች በአጽንዖት የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.