በአማራ ክልል ከመስኖ ልማት 47 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም በመስኖ ከሚለማው እርሻ 47 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታስቦ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ክልሉ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት አቅም እንዳለው ቢታመንም እስከ አሁን የለማው ከ11 በመቶ እንደማይበልጥ ይነሳል፡፡
በ2017 ዓ.ም 342 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የታቀደ ሲሆን÷ በዚህ ሥራም ከ1 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
በቢሮው የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና መስኖ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው እንዳሉት÷ በ2017 ዓ.ም 342 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 47 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ወደ ተግባር ተገብቷል።
ከዚህ ውስጥ 230 ሺህ ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር የመስኖ ስንዴ እንደሚለማ ጠቁመው÷ 8 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜም በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 54 ሺህ 984 ሄክታሩ ታርሷል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ውስጥም 34 ሺህ 621 ሄክታሩ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን፤ ከታረሰው ውስጥ 24 ሺህ ሄክታሩ ለስንዴ መታረሱን እና 1 ሺህ 861 ሄክታሩ በስንዴ ሰብል መሸፈኑን አብራርተዋል፡፡
ከ20 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያለሙ 5 ሺህ አዲስ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን የማሠራጨት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
እስከ አሁንም ከ3 ሺህ በላይ ያህሉ ወደ አርሶ አደሮች መሠራጨታቸውን እና ከ36 ሺህ በላይ ነባር የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ደግሞ ሌላው የልማቱ አቅም መሆናቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት የተጠናቀቁ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ መካከለኛ እና አነስተኛ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ሌላ ግብዓቶች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
1 ሺህ 857 ኪሎ ሜትር የቦይ ጠረጋ ሥራም እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡