የጤናውን ዘርፍ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንሰራለን – ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት የጤናውን ዘርፍ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ በየደረጃው በቁርጠኝነት የምንሰራ ይሆናል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናገሩ።
“የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ እምርታ ለተፋጠነ የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 26ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቅቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ባደረጉት ንግግር ጉባኤው በዘርፉ ያሉ ጥንካሬዎችና ክፍተቶች የተለየበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ዘርፉን ለማሻሻል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ የታየበት ጉባኤ እንደነበረም ተናግረዋል።
በጀት ዓመቱ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ላይ እምርታን ለማምጣት በርካታ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅብናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ዕቅዶችን ወደ ታች አውርደን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የጤና ኤክስቴንሽንን ማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ የመድሀኒት አምራቾችን ማጎልበት፣ የወባና ሌሎች በሽታዎችን መስፋፋት መቀነስ እና ሌሎችም የጤና ዘርፉን የሚያሻሽሉ ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመዋል።
ቀጣዩ የ2018 ዓ.ም የጤናው ዘርፍ ጉባኤ በጅማ ከተማ እንዲካሄድ መወሰኑም ተመላክቷል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ