አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን ከሁለት ቀናት በኋላ ይረከባል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 የተሰኘውን የመንገደኞች አውሮፕላን ከሁለት ቀናት በኋላ ይረከባል፡፡
አየር መንገዱ ከኤር ባስ ኩባንያ የሚረከበው ”Ethiopia Land of Origins” በሚል መጠሪያ የተሰየመው ኤ350-1000 አውሮፕላንም በዓይነቱ ልዩና በአፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑን ተነስቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ÷ አየር መንገዱ በአፍሪካ የአቪዬሽን መስክ ያለውን የቀዳሚነት ስፍራ ለማስቀጠል በየጊዜው አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስመጣትና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን በማስፋት ላይ እንደሚገኝ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
አየር መንገዱ ኤ350-900 አውሮፕላኖችን መጠቀም ከጀመረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ÷ አሁን ላይ 20 የኤ350-900 አውሮፕላኖች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ኤ350-1000 አውሮፕላን ደግሞ 400 መቀመጫዎች ያሉትና ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያስረዱት።