Fana: At a Speed of Life!

የኮሪደር ልማት ሥራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነው- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማው የተመረጡ ኮሪደሮችን መልሶ ለማልማት በተዘጋጀ ዕቅድ ላይ ከካባኔያቸው እና ወረዳ አመራሮች ጋር መክረዋል።

የመልሶ ልማት ዕቅዱ በመድረኩ ላይ ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን÷ የኮሪደር ልማት ስራው ለማህበረሰቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ ገልፀዋል።

ካሁን ቀደም የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ጠንክሮ መስራት ከተቻለ ሀገርን መቀየር እንደሚቻል በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኮሪደር ልማት ስራ ዋና አላማ ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎችን በመፍጠር የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እና ዘላቂ አካባቢዎችን መፍጠር መሆኑንም አመላክተዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው ከ1 ሺህ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረችው ዕድሜ ጠገቧ ሀረር ከተማ የሚመጥናትን እድገት እውን ለማድረግ እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በቀጣይ የኮሪደር የመልሶ ልማት ለማከናወን የተለዩ አካባቢዎችን በተመለከተ መንግስት ማህበረሰቡን የማፈናቀል ፍላጎት እንደሌለው ጠቁመዋል።

መልሶ ልማት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡ ባለበት ቦታ ይዞታውን እንዲያለማ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ጠቅሰው÷ ነዋሪውን ወደ ተቀያሪ ቦታ ማዛወር የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሐረሪ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.