አቶ ኦርዲን በድሪ 2ኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በይፋ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቀቱ እንደገለፁት÷ በክልሉ በከተማና በገጠር እንዲሁም በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ባጠቃላይ በሶስት ዘርፎች የኮሪደር ልማት ስራው ይከናወናል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ፣ ተሽከርካሪ፣ ሳይክል እና የመንገድ መብራቶችን አካቶ የአካባቢን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንደሚከናወንም አስገንዝበዋል።
በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ የገጠር ወረዳዎች መካተታቸውን ጠቁመው፤ የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረጉ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።
ሐረር እድሜ ጠገብ ከተማ ብትሆንም ዕድሜዋን በሚመጥን መልኩ ሳትለማ መቆየቷን አስታውሰው÷ የኮሪደር ልማቱ በቁጭት እና ተነሳሽነት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ካሁን ቀደም በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ማህበረሰቡን በስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውሰው÷ ነዋሪው ለልማት ስራው አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝ መግለፃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡