በሩብ ዓመቱ ከ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ከ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሶስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የሚገመግም ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ እንደገለጹት÷ በሩብ ዓመቱ ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የተለያዩ ሼዶችና የለማ መሬት ተላልፏል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ኢንቨስት ካደረጉት ባለሃብቶች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የቻይና፣ የጃፓንና የቬትናም ባለሀብቶች ከተሳቡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ኢንቨስት ያደረጉት ባለሃብቶች በሐዋሳ፣ ኮምቦልቻ፣ ቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የተሰማሩ መሆናቸው መገለጹን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።
መንግስት በዘርፉ የወሰደው ማበረታቻ፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተሰጠዉ ትኩረት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የኮርፖሬሽኑ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ለተገኘው ውጤት አስተዋፅኦ ማድረጉ ተነግሯል።
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሦስት ወራት ከ864 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱም ተገልጿል፡፡
ገቢውን የተገኘው ከማምረቻ ሼዶችና የለማ መሬት ኪራይ፣ ከአፓርትመንቶች እና ሕንጻዎች ኪራይ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮቹና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና በሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ሠመራ፣ ቂሊንጦ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በገቢ አፈጻጸም በግንባር ቀደምነት ተጠቅሰዋል፡፡