Fana: At a Speed of Life!

በጉባዔው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መፍትሔ ይቀርባል- አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚቀርቡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ጉባዔውን አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና በተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የግብርና ንግድ እና መሠረተ ልማት ዳይሬክተር ደረጀ ተዘራ ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት÷ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለሚካሄደው ለዚሁ ጉባዔ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡

ጉባዔው የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግርን በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንደሚያስቀምጥም አመላክተዋል፡፡

ይህ ጉባዔ ኢትዮጵያ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና ቱሪዝም ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የምታስተዋውቅበት ዕድል እንደሚፈጥርም ነው ያስገነዘቡት፡፡

አቶ ደረጀ በበኩላቸው÷ ዓለምን ብሎም አፍሪካን እየፈተነ ያለው የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ለከፋ ችግር እና እንግልት እየዳረገ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የዓለም የምግብ ዋስትናን ችግር ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው÷ ጉባዔው ይህንን ለማስገንዘብ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ምሁራን፣ የግል ሴክተሮች፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በጉባዔው እንደሚሳተፉ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

በምንተስኖት ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.