Fana: At a Speed of Life!

19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅበረብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱን በሚያጸና መልኩ ማክበር ይገባል- አፈ ጉባዔ አገኘሁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅበረብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱን በሚያጸና መልኩ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴና የማኔጅመንት አባላት የበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አፈጻጸም ገምግመዋል፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት ÷የዘንድሮውን በዓል የሚያስተናግደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኅብርና በአብሮነት የሚኖሩበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዓሉ ኅብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር እና ክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት በሚያስተዋውቅ ደረጃ እንደሚከበር አስገንዝበዋል፡፡

በክልል ደረጃ የሚከበሩ የበዓል ዝግጅቶችም በሕዝቦች መካከል ወዳጅነትንና አብሮነትን በሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በዓሉን አስመልክቶ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸው በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናከሩ፣ የልማት ሥራችን የሚያፋጥኑና የወል ትርክቶች በዜጎች ዘንድ እንዲሰርጹ የሚያደርጉ የአስተምህሮ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑም ተገልጿል፡፡

19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ አንድነት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንደሚከበር የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.