Fana: At a Speed of Life!

በዎላይታ ዞን በከተሰተው የመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እየቀረበ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዎላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የአደጋ ሥጋት አመራር ጽሕት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ ሥምንት ወረዳዎች ለመሬት መንሸራተትና ናዳ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የአደጋ ሥጋት አመራር ጽሕት ቤት ኃላፊ ዳዊት ዳሳለኝ  አስታውቀዋል፡፡

በዚህም 800 አባዎራዎችን እንደገና ለማደራጀት እየተሠራ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

በአካባቢዎቹ አሁንም ከባድ ዝናብ መኖሩን ገልጸው÷ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ጥናት በማካሄድ ሌላ አማራጭ ቦታ ለማዘጋጀት በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

በዞኑ ካዎ ኮይሻ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች ትናንት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሰባት ወገኖች ሕይወት ማለፉ እና በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድሱ ተገልጿል፡፡

በዚሁ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችም ጊዜያዊ መጠለያን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ድጋፎች እየቀረቡላቸው መሆኑን ነው አቶ ዳዊት ያረጋገጡት፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ የመሬት መንሸራተት አደጋው በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ባደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሐዘን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

አደጋው ሙሉ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ የሰባት ወገኖችን ሕይወት መቅጠፉንም አስታውቀዋል፡፡

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.