ምክር ቤቱ ነገ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል፡፡
በመደበኛ ስብሰባው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
ይህን ተከትሎም ምክር ቤቱ የመንግስትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዕለቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስብሰባው ይገኛሉ፡፡
የስብሰባው ሙሉ ሒደት በቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ እንደሚተላለፍም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡