Fana: At a Speed of Life!

ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል የተጠረጠሩ የመዲናዋ ገቢዎች ቢሮ ኦዲተሮችን ጨምሮ 24 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከግብር ከፋዮች ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የተጠረጠሩ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኦዲተሮችን ጨምሮ 24 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ እና በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብ ወንጀል ክስ በየደረጃው መስርቶባቸዋል።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ኦዲት ቡድን አስተባባሪ ሃብታሙ ግዲሳ ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ስምረት ገ/እግዚአብሔር ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር አቤኔዘር ቶሎሳ ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋይ የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ለሚ ሲሌ እና ወ/ሮ መቅደስ ታደለን ጨምሮ በየደረጃው ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 24 ግለሰቦች ናቸው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት የጉቦ መቀበል ሙስና ወንጀል በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከመስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ከግብር ከፋይ ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከግብር ከፋይ ከተለያዩ ድርጅቶች፣በተለያዩ መጠኖች ጉቦ ተቀብለዋል በማለት የምርመራ ማጣሪያ ስራ ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል።

ይህ ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተሰጠው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ መሰረት ክሱን አዘጋጅቶ ዛሬ በመደበኛው ችሎት የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቧል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የሃብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ባደረገው የማጣራት ሥራ በተወሰኑ ተከሳሾች ጉቦ በመቀበል የተገኘ ገንዘብን ተከትሎ የማይንቀሳቀሱ 3 የሪል እስቴት መኖሪያ ቤቶች እና 1 ቪላ መኖሪያ ቤት በማግኘት ንብረቱ እንዲታገድ ያደረገ ሲሆን÷ የሃብት ማጠራት ሥራ መቀጠሉም ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ የቀረበባቸውን ክስ የተወሰኑ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ የዋስትና ክርክርን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ለነገ በይደር ቀጠሮ ይዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.