የብሔራዊ ባንክ የዋሽንግተን ቆይታ ስኬታማ ነው – አቶ ማሞ ምኅረቱ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ያደረገው ቆይታ ግቡን የመታና ስኬታማ መሆኑን የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ያካተተ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ በዋሽንግተን ዲሲ ባዘጋጁት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተሳትፏል፡፡
የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በስብሰባው የነበራቸውን ቆይታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ በስብሰባው ወቅት የዓለም ኢኮኖሚ በ2024 እና 2025 በ3 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ በስብሰባው ላይ መገለጹን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ማዕከላዊ ባንኮች በወሰዱት የተቀናጀ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ምክንያት እየተረጋጋ ቢሆንም÷ አሁንም የኑሮ ውድነት ከፍ ያለ እንደሆነና በዋጋ ንረት ላይ በተከናወኑ ተግባራት ስኬት መገኘቱም ተነስቷል ብለዋል፡፡
እንደ ትልቅ ስጋት ከሚታዩት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥት እዳ መጨመሩ፣ የጂኦ ፖለቲካ መከፋፈል እና የንግድ ክልከላዎች መስፋፋት የዓለም ኢኮኖሚን እድገት በመካከለኛ ጊዜ እንደሚጎዳው መነሳቱንም አብራርተዋል፡፡
በሀገራት መካከል ትብብርን ማስፋት፣ የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ፣ጠንቃቃ የገንዘብ ፖሊሲ መከተል እና እድገትን የሚደግፉ መዋቅራዊ እርምጃዎችን መውሰድ የሀገራትን እድገት ዘላቂ ሊያደርግ እንደሚችልም መገለፁን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ መድረክ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ ልዑክ ከበርካታ ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊ እና አካባቢያዊ ተቋማት ጋር መምከሩን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ልዑኩ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኃላፊዎች፣ ከማዕከላዊ ባንኮች፣ ከውጭ ባንኮችና ከባለሃብቶች ጋር መምከሩን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ለእነዚህ ተቋማት እየተወሰዱ ስላሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች፣ በብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እየተደረጉ ስላሉ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍና የውጭ ምንዛሪ አሥተዳደር ፋይዳዎችና ትሩፋቶች እንዲሁም በሪፎርሙ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን ለመቀነስ ስለተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች ገለፃ አድርገናል ብለዋል፡፡
ድርጅቶቹም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ አቅጣጫ በአድናቆትና በተምሳሌትነት እንደሚመለከቱትና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጣቸውን አቶ ማሞ አመላክተዋል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቆይታ የተሳካ እና የኢትዮጵን ገፅታ ለመገንባት የሚጠቅም ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋት የሚረዳና የኢትዮጵያ መንግሥት ለጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡