Fana: At a Speed of Life!

ማሻሻያው ግልፅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ፓርቲዎችን ወደፖለቲካ ምህዳሩ ለማምጣት ያለመ ነው – ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተሻሻለው የፓርቲዎች የምዝገባና ሰነድ ማሻሻያ ክፍያ ግልፅ ዓላማ ያላቸውን ፓርቲዎች ወደ ፖለቲካ ምህዳሩ ለማምጣት ያለመ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 67/4/ሀ-ለ/ መሰረት የምዝገባ ጥያቄ ያቀረበ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም የመሰረታዊ ሰነዶች ማሻሻያ ያደረገ ፓርቲ ክፍያ እንደሚፈጽም ተቀምጧል።

በአንቀጽ 67/6/ ደግሞ የክፍያ መጠኑም በቦርዱ እንደሚወሰንም ተደንግጓል፡፡

በዚሁ መሰረት ሀገር አቀፍና ክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ የምስክር ወረቀት ለማግኘት 100 ብር እና ሙሉ እውቅና ለማግኘት 200 ብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን የቦርዱ መረጃ ያሳያል።

የተመዘገቡ ፓርቲዎች መሰረታዊ ሰነዶቻቸውን በጉባኤ አሻሽለው ሲያቀርቡ 30 ብር የአገልግሎት ክፍያ ይከፍሉ እንደነበርም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብእሸት አየለ በሰጡት ማብራሪያም ፥ ቦርዱ ፓርቲዎች የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ላይ ከጥቅምት 11/2017 ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን ማሻሻያ ማድረጉን ገልጸዋል።

ቦርዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች መከተል በሚገባቸው ሕግጋት፣ የፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ሌሎችም ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በዚሁ መሰረት የጊዜያዊ እውቅና ክፍያ ወደ 15 ሺህ ብር፣ የሙሉ እውቅና ክፍያ 30 ሺህ ብር እንዲሁም የሰነድ ማሻሻያ ክፍያው ወደ 5 ሺህ ብር ከፍ ማለቱንም ነው ያነሱት።

“አንድ አንድ ፓርቲዎች በፓርቲነት የሚመዘገቡት በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አሻራ ለማኖር ሳይሆን ተያያዥ ጥቅሞችን በማሰብ መሆኑን ተገንዝበናል” ሲሉም ገልጸዋል።

“በአግባቡ የሚታገሉ፣ ከድጎማ ፖለቲካ የተላቀቁ ፓርቲዎችን ማበረታታት ይገባል” ያሉት አቶ ውብእሸት ፥ ቦርዱ የክፍያ ማሻሻያ ያደረገው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ ሳይሆን ግልፅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸውን ፓርቲዎች ወደ ፖለቲካ ምህዳሩ ለማምጣት እንደሆነም አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሴቶችን ተሳትፎ ለማበረታት በማሰብ ከቦርዱ የሚመደበውን ገንዘብ አላግባብ በወሰዱ ፓርቲዎች ላይ የእግድ እርምጃ መወሰዱንም አስረድተዋል።

ቦርዱ በፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሴቶችን እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ለማበረታታት ለፓርቲዎች ገንዘብ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱን መግለጻቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።

ይሁን እንጂ ለማበረታቻ ከቦርዱ የሚበጀተውን ገንዘብ አላግባብ ለመጠቀም የሌላቸውን አባላት ቁጥር አለን በማለት የሚያቀርቡ ፓርቲዎች መኖራቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ቦርዱ ባደረገው ማጣራት የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የሌላቸውን ሴት አባላት ቁጥር አለን በማለት የሃሰት ሪፖርት በማቅረብ ገንዘብ በመቀበል ህገ-ወጥ ተግባር በመፈጸማቸው የዕግድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው አብራርተዋል።

እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ ፥ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ላይ እርምጃውን የወሰደው በህጉ መሰረት ፓርቲዎች አሉ ስለተባሉት ሴት አባላት ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.