Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልዑክ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ሞሊ ፊ እና ከአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ብረንት ኒማን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ አቶ አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ ስላለው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዲሁም በመንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በቡድን 20 አባል ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ የእዳ አያያዝ ድርድር ለማድረግ በምታደርገው ጥረት የልማት አጋሮች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ መንግስት የወሰደውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሉዓላዊ የዕዳ ድርድር መሰረት የእዳ አያያዝ ስምምነት ለማድረግ በምታደርገው ጥረት አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያና የአሜሪካ የሁለትዮሽ እና ባለ ብዙ ወገን ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.