Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ከብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያን ሰጥቶ በመቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት አንጸባርቀዋል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት የኢትዮጵያን በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት ፍላጎትንና አቋም ማንጸባረቃቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን የተሳተፉበት 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በሩሲያ ካዛን ከተማ መካሄዱ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንዳለባት እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ አካተች እንዲሆን ያቀረቡትን ጥሪ ጉባዔው ተቀብሎ የጋራ አቋም እንደያዘበትም አብራርተዋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች የኢትዮጵያን አቋሞች ማንጸባረቅ እንደተቻለም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወደብ አኳያ ኢትዮጵያ ከታሪክም፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የሕዝብ ብዛት እና የኢኮኖሚ እድገቷን የሚመጥን የባህር በር ማግኘት እንደሚገባት ከሀገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይቶች ላይ ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋን የሰጥቶ መቀበል መርህን መሰረት ያደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቶቻቸው በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ ማሻሻያ እንዲደረግ ያቀረቡት ሀሳብ በሌሎች ሀገራትም ተቀባይነት ማግኘቱንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በመድረኩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ተቋማት ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የምታደርጋቸውን ማሻሻያዎች አስመልክቶም ገለጻ መደረጉንም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ ከታሰበው በላይ በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ግንዛቤ የተወሰደበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች እና የተያዙ የጋራ አቋሞች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች የሚያሳኩ ሆነው መገኘታቸውን ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.