መከላከያ ሠራዊት የአንድነት መሠረት ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራዊ አንድነታችን መሠረቱ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የቆመ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስገነዘቡ፡፡
117ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ከፍተኛ የመንግሥትና የሠራዊቱ አመራሮች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር÷ የሀገራዊ አንድነታችን መሠረቱ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የቆመ ነው፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የከፈሉት መሥዕዋትነት ደግሞ ለዚህ ሂደት ያልተቋረጠ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመከላከያ ሠራዊቱ ፀንታ መቆሟን ጠቅሰው÷ ይህም ምንጊዜም ሲዘከር የሚኖር ሐቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ÷ ሠራዊቱ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ከሀገርም ባለፈ ለአፍሪካ ምሣሌ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ገድል በኢትዮጵያውያን ልብ የታተመ እንደሆነ አንሥተው÷ የዘወትር ዝግጁነቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በዓለምሰገድ አሳዬ እና ሶሎሞን ይታየው