እስራኤል አዲሱን የሂዝቦላህ መሪ ሀሽም ሳፊይዲንን መግደሏን አረጋገጠች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሀሰን ናስራላህ ምትክ ወደ ቡድኑ ሀላፊነት መጥቶ የነበረውን የቡድኑን መሪ ሀሽም ሳፊይዲንን መግደሏን አረጋገጣለች፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሃይል እንዳስታወቀው÷ የቀድሞው የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ የአጎት ልጅ የሆነው ሀሽም ሳፊይዲን ከሶስት ሳምንት በፊት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በወሰደችው የአየር ጥቃት ተገድሏል።
ከሀሽም ሳፊይዲን በተጨማሪ የሂዝቦላህ ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ሃላፊ አሊ ሁሴን ሃዚማ እና የቡድኑ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በጥቃቱ ተገድለዋል ተብሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሂዝቦላህ የሰጠው ምላሽ አለመኖሩ ተገልጿል።
ቀደም ሲል በፈረንጆቹ ጥቅምት 8 ቀን 2024 የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የእስራኤል መከላከያ ሀይል ሀሰን ሳፊይዲንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የሂዝቦላህ መሪዎችና ታጣቂዎች መገደላቸውን ተናግረው ነበር።
በወቅቱም ሀሰን ነስራላህን በመተካት ወደ ሂዝቦላህ መሪነት የመጣው ሀሽም ሳፊይዲን ሳይገደል እንዳልቀረ እየተነገረ ነበር።
ይሁን እንጂ በእስራኤል ጥቃት የመሪውን መገደል የእስራኤል መከላከያ ሃይል አዛዥ ሌተና ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።